በመርካቶ ያለ ደረሰኝ በሚሸጡ አስመጪዎችና አከፋፋዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ 58 የቁጥጥር ቡድኖች ተሰማሩ

በመርካቶ ያለ ደረሰኝ የሚገበያዩ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን መሰማራታቸው ተገልጿል

Nov 15, 2024 - 21:25
 0  18
በመርካቶ ያለ ደረሰኝ በሚሸጡ አስመጪዎችና አከፋፋዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ 58 የቁጥጥር ቡድኖች ተሰማሩ
  • ቡድኖቹ እስከ መቶ ሺሕ ብር ቅጣት የመጣል ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል

በመርካቶ ገበያ ያለ ደረሰኝ የሚሸጡ ነጋዴዎችን በተለይ አስመጪዎች፣ አምራቾችና አከፋፋዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ቁጥጥር የሚያደርጉ ከሦስት እስከ አምስት አባላትን የያዙ 58 ቡድኖች መሰማራታቸው ተገለጸ።

ሰኞ ኅዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም. በግዙፉ የገበያ ሥፍራ መርካቶ ‹‹ንብረት ይወረሳል›› የሚል መረጃ መሠራጨቱን ተከትሎ ውዝግብ ተፈጥሮ ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ በዕለቱ የተከሰተውን አለመረጋጋት በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፣ በመርካቶ ሕገወጥ ነጋዴዎች ላይ ቁጥጥር ከማድረግ ያለፈ ንብረት የመውረስ ዕርምጃ እንዳልተወሰደ በመግለጽ ማኅበረሰቡ እንዲረጋጋ አሳስቦ ነበር። 

ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሰውነት አየለ ከዚህ በፊትም በመርካቶ በሕገወጥ ነጋዴዎችና በሕገወጥ ግብይት ላይ ቁጥጥር እንደሚደረግ አስታውሰው፣ ሰሞኑን የተጀመረውን የቁጥጥር ዕርምጃ ለየት የሚያደርገው አዳዲስ ተቆጣጣሪዎች እንዲሰማሩ መደረጉ ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል። 

ከዚህ ቀደም በመርካቶ ገበያ ቁጥጥር እንዲያደርጉ የተሰማሩ ተቆጣጣሪዎች ከነጋዴዎች ጋር በመላመድና ጉቦ በመቀበል ወቀሳ ይቀርብባቸው ስለነበር፣ ቀደም ሲል የነበሩትን የቁጥጥር ባለሙያዎች ሙሉ በሙሉ ከዚህ ሥራ እንዲወጡ በማድረግ በአዲስ መተካታቸውን አስረድተዋል። አዲሶቹ ተቆጣጣሪዎች ከዩኒቨርሲቲ የወጡ ምሩቃን መሆናቸውን፣ የተወሰነ ሥልጠና ወስደው እንዲሰማሩ መደረጉን ጠቁመዋል።

እነዚህ ከዩኒቨርሲቲ የወጡ ምሩቃን የተወሰነ ሥልጠና ወስደው ከአንድ ልምድ ያለው ተቆጣጣሪ ጋር በማጣመር፣ ከሦስት እስከ አምስት አባላትን በያዙ 58 ቡድኖች ተዋቅረው መሰማራታቸውን ተናግረዋል።

እነዚህ ቡድኖች በተመደቡባቸው አካባቢዎች ላይ ያለ ደረሰኝ ግብይት የሚፈጽሙ ነጋዴዎችን በመለየት እስከ 100 ሺሕ ብር ቅጣት ያለው ዕርምጃ እንዲወስዱ ኃላፊነት የተሰጣቸው መሆኑን፣ በተመደቡባቸው አካባቢዎች ለሚፈጸሙ ሕገወጥ ግብይቶች ተቆጣጣሪዎቹ ኃላፊነት እንደተጣለባቸውም አስረድተዋል።

ኃላፊው አክለውም፣ ከዚህ ቀደም በችርቻሮ ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ ብቻ ትኩረት ያደርግ የነበረውን የቁጥጥር ሥርዓት በመለወጥና በማስፋት ከአምራቾች፣ አከፋፋዮችና አስመጪዎች አካቶ ወደታች እስክ ችርቻሮ ነጋዴዎች እንዲወርድ መደረጉን አብራርተዋል።

ሰኞ ዕለት በተጀመረው ጥብቅ ቁጥጥር እስካሁን ድረስ ምን ያህል ነጋዴዎች እንደተቀጡ ለቀረበላቸው ጥያቄ አኃዛዊ መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል።

ጥብቅ የተባለው ቁጥጥር ከመጀመሩ አስቀድሞ ከመርካቶ ነጋዴዎች ጋር በተለይም በችርቻሮ ንግድ ከተሰማሩት ጋር ውይይት ተደርጎ እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊው፣ በውይይቱም በችርቻሮ ንግድ የተሰማሩ ምርቶችና ሸቀጦችን ከአስመጪዎች፣ ከአምራቾችና ከአከፋፋዮች በሚረከቡበት ወቅት ደረሰኝ እንደማይሰጧቸው ማሳወቃቸውን ገልጸዋል።

ይህንንም መሠረት በማድረግ በመርካቶ ገበያ ዋና አከፋፋዮች፣ አምራቾችና አስመጪዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ መወሰኑን፣ በመስከረምና በጥቅምት ወራትም በምርት መነሻዎች ላይ ማለትም አስመጪዎች፣ አምራቾችና አከፋፋዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ቁጥጥር ሲደረግ መቆየቱን ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ ከሰሞኑ የተጀመረውን የቁጥጥር ሥራ ተከትሎ ተቆጣጣሪ አባል መስለው የማጭበርበር ድርጊት የጀመሩ ሰዎች ስለመኖራቸው ጥቆማዎች መድረሳቸውን የገለጹት አቶ ሰውነት፣ ይህንን ለመከላከል ደግሞ ነጋዴዎችና ሸማቾች ጥቆማ የሚሰጡበት 7075 ነፃ የስልክ መስመር መዘጋጁትን አስረድተዋል። አክለውም፣ የገቢዎች ቢሮው ያሰማራቸው የቁጥጥር ባለሙያዎች ሱቅ ውስጥ እንደማይገቡና ሽያጭ ብቻ እንደሚቆጣጠሩ ገልጸዋል። 

What's Your Reaction?

like

dislike

love

funny

angry

sad

wow