በርካታ አገሮች ኢትዮጵያ የሞት ቅጣትን እንድታስቀርና በትዳር ውስጥ የሚፈጸም አስገድዶ መድፈር ድርጊት ወንጀል ሆኖ እንዲደነገግ ጠየቁ

በርካታ አገሮች ኢትዮጵያ የሞት ቅጣትን እንድታስቀርና በትዳር ውስጥ የሚፈጸም አስገድዶ መድፈር ድርጊት ወንጀል ሆኖ እንዲደነገግ ጠየቁ

Nov 13, 2024 - 13:02
 0  12
በርካታ አገሮች ኢትዮጵያ የሞት ቅጣትን እንድታስቀርና በትዳር ውስጥ የሚፈጸም አስገድዶ መድፈር ድርጊት ወንጀል ሆኖ እንዲደነገግ ጠየቁ
  • በአማራና አሮሚያ ክልል እየተፈጸመ ያለ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል
  • መንግሥት በአማራ ክልል የተከፋፋለ ዕዝ መኖሩ ለሰላም ሒደቱ አስቸጋሪ ሆኗል ብሏል

በስዊዘርላንድ ጄኔቫ እየተካሄደ ባለው አራተኛው ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ግምገማ ኢትዮጵያን በተመለከተ አስተያየት ከሰጡ 117 አገሮች መካከል በርካቶቹ ኢትዮጵያ የሞት ቅጣትን እንድታስቀር፣ በትዳር ውስጥ የሚፈጸም አስገድዶ መድፈር በወንጀል እንዲያስቀጣ እንዲሁም በአማራ፣ በኦሮሚያና ሌሎች አካባቢዎች በቀጠለው ጦርት የበዛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲቆም ጠየቁ፡፡

በተመሳሳይ ሕፃናትን ለወታደር የመመልመል፣ በጋዜጠኞች፣ በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ በሲቨክ ማኅብረሰብ ድርጅቶችና ተቃዋሚ በፖለቲካ ኃይሎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና ከሕግ ውጪ የሚፈጸሙ እስሮች እንዲቆሙ ጠይቀዋል፡፡

ኅዳር 3 ቀን 2017 ዓ.ም. በተካሄደውና ከሦስት ሰዓት በላይ በፈጀው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ግምገማ በርካታ አገሮች ምክረ ሐሳብ አቀርበዋል፡፡ የሞንቴኔግሮ ተወካይ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ ሕፃናትን ለወታደራዊ ተልዕኮ መመልመል ተግባራት እንዲቆሙና በትዳር ውስጥ የሚፈጸም የአስገድዶ መድፈር ተግባር ወንጀል ሆኖ እንዲደነገግ እንዲሁም የሞት ፍርድ እንዲሻር ጠይቀዋል፡፡

የሞንጎሊያው ተወካይ ኢትዮጵያ አስገድዶ መሰወር ድርጊትን የሚከላከለውን ዓለም አቀፍ ሕግ እንድታፀድቅና የሞት ፍርድን እንድትሽር፣ የሞሮኮው ተወካይ ደግሞ በማቆያ ቦታዎች ኢሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ቁጥጥር እንዲዘረጋ ጠይቀዋል፡፡

ሞዛምቢክ በጦርነት አካባቢዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲከበርና ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ፣ ጋምቢያ የሞት ፍርድን የሚያስቀረው የዓለም አቀፍ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ተጨማሪ ፕሮቶኮል እንዲፀድቅ ምክረ ሐሰብ አቅርበዋል፡፡

ቶጎ፣ ታይላንድ፣ ኒውዝላንድና ሌሎችም አገሮች በበኩላቸው በኢትዮጵያ የማሰቃየት፣ የግድያ፣ አስገድዶ መሰወርና በመደበኛና መደበኛ ባልሆኑ የፌዴራል ማቆያ ቦታዎች ከሕግ ውጭ የሚደረጉ አያያዞች ገለልተኛ በሆኑ አካላት እንዲመረመር ጠይቀዋል፡፡ አክለውም ቀደም ሲል ጦርነቱ በተካሄደባቸው ሰሜን ኢትዮጵየና አሁን ጦርነት ውስጥ ባሉ አካባቢዎች ላይ የደረሱና እየደረሱ ያሉ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን በተመለከተ መንግሥት ዕርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡

ኒውዝላንድ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የመሰብሰብ መብት እንዲከበር ስትጠይቅ፣ ኖርዌይ ደግሞ በትግራይ፣ በአማራና በሌሎች አካባቢዎች እየታዩ ያሉ የመብት ጥሰቶች እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል፡፡ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ከዓለም አቀፍ የሕግ ተጠያቂነት ጋር በማገናኘት ተግባራዊ እንዲደረግ የጠየቁት የኖርዌይ ተወካይ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የመሰብሰብ መብት እንዲከበር፣ የጋዜጠኞችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾ መብት ላይ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት የሚፈጽሙት ጥሰት እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡

ፈረንሣይ፣ ኢስቶኒያ፣ ዩክሬን፣ ፖላንድና ፖርቱጋል በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ የሞት ቅጣቱን የሚከለክለውን ዓለም አቀፍ የሲቪል የፖለቲካ ሕግ ስምምነት እንድታፀድቅ ጠይቀዋል፡፡

ፖርቱጋል ትዳር ውስጥ የሚፈጸምን አስገድዶ መድፈር ድርጊት በወንጀል የሚያስጠይቅ ሆኖ እንዲደነገግ የጠየቀች ሲሆን፣ የሐሳብ ነፃነት እንዲረጋገጥ ጋዜጠኞች ከጥቃትና ጉዳት እንዲጠበቁ የጠየቁት ደግሞ የደቡብ ኮሪያ ተወካይ ናቸው፡፡

የስሎቫኪያ ተወካይ በአማራ፣ ኦሮሚያና ትግራይ አካባቢዎች የመብቶች ጥሰቶች አሳሳቢ መሆኑን ሲገልጹ ስፔን ለጋዜጠኞች፣ ለሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ለሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሊያሠራ የሚችል ምኅዳር እንዲፈጠር ምክረ ሐሳብ አቅርባለች፡፡

የስዊድን ተወካይ በኢትዮጵያ በቀጠለው ጦርነት እየተፈጸሙ ያሉትን የመብቶች ጥሰቶችና የሰብዓዊ ዕርዳታ ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ያሳስበናል ብለዋል፡፡ አክለውም ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ የሽግግር ፍትሕ እንዲከናወን ጠይቀዋል፡፡

በፌዴራልና ክልል ማቆያ ቦታዎች ተፈጽመዋል የተባሉ የማሰቃየት ተግባራት በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ስዊዘርላንድ ጠይቃለች፡፡

የአሜሪካ ተወካይ በሰሜን ጦርነት ላይ ለተፈጸመው የጦር ወንጀሎች  ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፤ በአማራ፣ ኦሮሚያ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች እየተፈጸሙ ያሉ የመብት ጥሰቶች በእጅጉ እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል፡፡ አክለውም መሠረታዊ ነፃነቶች በአገሪቱ መገደባቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡

 የመናገርና የመሰብሰብ ነፃነት መገደቡን፣ ጋዜጠኞች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ተቃዋሚ ኃይሎች መብታቸውን በመተገበራቸው ምክንያት የታሰሩ አካላት ከታሰሩበት እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡ በተጨማሪም ለዓለም አቀፍና ለአገር ውስጥ የሰብዓዊ መብት መርማሪዎች አገሪቱ ያልተገደበ የምርመራ ፈቃድ እንድትሰጥ ጠይቀዋል፡፡

የአውስትራሊያ ተወካይ በአማራና ኦሮሚያ ክልል እየተካሄዱ ባሉ ጦርነቶች   ከፍተኛ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳሳሰባቸው ሲገለጹ፣ የኦስትሪያ ተወካይ በበኩላቸው፣ በቁጥጥር ሥር ያሉ ዜጎች ኢሰብዓዊ አያያዝ አስገድዶ የመሰወር ተግባርና የመሳሰሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶት አሳሰቢ ስለመሆናቸው አስታውቀዋል፡፡

የመንቀቀስና የመሰባሰብ መብት እንዲጠበቅ፣ የጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ያለምንም ማስፈራሪያ ዛቻና ከሕግ አግባብ ውጪ ከሚደረግ እስር ነፃ ሆነው ሥራቸውን እንዲሠሩ ጠይቀዋል፡፡

ካናዳ በበኩሏ፣ በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ገለልተኛ የሆነ የዳኝነት አካል እንዲቋቋም፣ አንዲሁም አሁን በአማራና ኦሮሚያ በቀጠለውን ጦርነት የሚታዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ እንዲታይ ጠይቀዋል፡፡

ዴንማርክ በበኩሏ፣ በትዳር ውስጥ የሚደረግ አስገድዶ መድፈር ተግባር በወንጀል የሚያስጠይቅ እንዲሆን የወንጀል ሕጉ እንዲሻሻል ስትጠይቅ፣ ጀርመን በአማራና በኦሮሚያ ቀጥሏል ባለችው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲሁም በጋዜጠኞችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች መታሰር የሚደርሰባቸው ጥቃት እንደሚያሳስባቸ ገልጸዋል፡፡

ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የፍትሕ ሚኒስትር ደኤታው አቶ በላይሁን ይርጋ፣ በአማራ ክልል ያለውን ጦርነት ለመፍታት በክልሉ በተቋቋመው የሰላም ካውንስል አማካይነት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው በመንግሥት በኩል ፍላጎት ቢኖርም በክልሉ ያለው ያልተደራጀና የተከፋፈለ የታጣቂዎች ዕዝ መኖር የሰላም ሒደቱን አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ከፍትሕ ሚኒስቴር የሄዱት የሥራ ኃላፊ አቶ የሱፍ ጀማው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለማንኛውም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ይሠራል ብለዋል፡፡ ተፈጽመዋል የተባሉ በርካታ የመብት ጥሰቶች ተጣርተው እስከ ዕድሜ ልክ እስር የተፈረደባቸው ወንጀለኞች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡

የአገር መከላከያ ሠራዊት የሠለጠነውና የሚመራው በዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግጋት መሠረት መሆኑ ጠቅሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ ታጣቂ ኃይሎች በተደጋጋሚ የንፁኃን መገኛ የሆኑ ትምህርት ቤቶች፣ የሃይማኖት ቦታዎችና የሕክምና ተቋማትን እንደ ወታደራዊ ካምፕ እየተጠቀሙ በመሆኑ የአገር መከላከያ ሠራዊት የተቸገረበት ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዳይሬክተር ረታ ዓለሙ (አምባሳደር) በበኩላቸው፣ በኮቮድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለምርመራ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ አካላትን ተቀብሎ ማስተናገድ ከባድ እንደነበር ጠቅሰው በቀጣይ የሚደረጉ ጉብኝቶች ካሉ አገሪቱ ለመተባበር ዝግጁ ናት ብለዋል፡፡

ከፍትሕ ሚኒስቴር የተወከሉት ሌላው የሥራ ኃላፊ አቶ አማኑኤል ታደሰ በበኩላቸው፣ በሰጡት መልስ በኢትዮጵያ ገለልተኛ የሆነ የሚዲያ ተቆጣጣሪ አካል መኖሩን ጠቅሰው፣ ሚዲያ ተቋማት ከአስፈጻሚው የመንግሥት አካል ነፃ መሆናቸውንና  አሁን ላይ 17 የኅትመት ሚዲያዎች፣ 21 የሕዝብ ሚዲያዎች፣ 31 የንግድ ሚዲያዎች፣ 38 የማኅበረሰብ ሚዲያዎች፣ 34 ሃይማኖታዊና 48 የድኅረ ገጽ ሚዲያዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

የሚዲያ ተቋማት ራሳቸውን በራሳቸው ቁጥጥር የሚያደርጉበት የኢትዮጵያ ሚዲያ ካውንስል የተሰኘ ተቋም መኖሩን ጠቅሰው ይህ ተቋም የጋዜጠኝነት ሚና እንዲያድግ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ስለመሆኑና የዴሞክራሲ ግንባታ ሒደትና የሚዲያ ነፃነት ምኅዳሩ እንዲሰፋ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል፡፡

What's Your Reaction?

like

dislike

love

funny

angry

sad

wow