ለቀድሞ ጦር አካል ጉዳተኞች መቐለ ላይ ቦታ ለመስጠት የቀረበው እቅድ ተቃውሞ ገጠመው
የመቐለ ከተማ አስተዳደር፣ ትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ፣ እስከ ኢትዮጵያ ኤርትራ ጦርነትና ከዛ በፊት በነበሩ ጦርነቶች ላይ ተሳትፈው የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ወደ 1ሺሕ 28 የሚደርሱ የቀድሞ የትግራይ ተወላጅ የጦር አባላት የመኖሪያ ቤት ቦታ ሊሰጣቸው መኾኑን ይፋ አድርጓል። ይህንን እቅድ የተቃወመው በአዲስ አበባ ተመስርቶ በቅርቡ ጽሕፈት ቤቱን መቐለ ከተማ የከፈተው ሰብዓ እንደርታ ፓርቲ ሲኾን፣ “ለጦር አካል ጉዳተኞች መኖርያ ቤት የሚሆን በሚል ሰበብ የመሬት ወረራ እየተፈፀመ ነው" ሲል አቤቱታውን አሰምቷል። አስተዳደሩ መሬቱን ለመስጠት ያቀደው ለትግራይ ጦር አካል ጉዳተኞች ማኅበር መቐለ ቅርንጫፍ አባለት መኾኑን የጠቀሱት የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አብርሀም ፅጌ ከዚኽ ቀደም ለጦር ጉዳተኞች መሬት መሰጠቱንን መከራከሪያ በማቅረብ የአኹኑን እቅድ ተቃውመዋል። የመቐለ ከተማ የመሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ ገብረሚካኤል እኑን፣ የጦር አካል ጉዳተኞች የመኖርያ ቤት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚደነግገውን ሕግ መሰረት አድርገው እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል። በቅርቡ ለጦር አካል ጉዳተኞች የመኖርያ ቤት መሬት ዕጣ ለማውጣት ታቅዶ የነበረው ተጨማሪ ማጣራት ስላስፈለገው ለሌላ ጊዜ እንደተራዘመም ተናግረዋል። (ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያገኛሉ)
What's Your Reaction?