የጀርመኗ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በኪየቭ ጉብኝታቸው ዩክሬንን መደገፋቸውን እንደሚቀጥሉ ተናገሩ
ከዩክሬን መሪዎች ጋር ተገናኝተው ለመነጋገር በዛሬው ዕለት ወደ ኪቭ ያቀኑት የጀርመኗ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አናሌና ቤርቦክ ሃገራቸው ዩክሬንን መደገፏን እንደምትቀጥል በመግለጽ ቃል ገቡ።ባርቦክ አክለውም ‘የሩስያ የአየር ድብደባ አይሎ ወደ ክረምቱ በዘለቀበት እና ሰሜን ኮሪያ ለሞስኮ የምትሰጠው ወታደራዊ ድጋፍ ተጨማሪ ስጋት እየደቀነ ባለበት ወቅት ዩክሬይን ከመቼውም የበለጠ ድጋፍ ያስፈልጋታል’ ብለዋል። ‘ዩክሬናውያን እየተፈጸመባቸውን የጭካኔ ድርጊት በሰብአዊነት እና በምንሰጠው ድጋፍ እየመከትን፤ ክረምቱን መሻገር ብቻ ሳይሆን አገራቸውም እንዲያተርፉ ጭምር እናግዛቸዋለን። በድፍን አውሮፓ ለምንገኝ ለሁላችንንም ነጻነት እየታገሉ ነውና” ብለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የሩስያ ኃይሎች ለሊቱን በበርካታ የዩክሬይን አካባቢዎች ላይ ካነጣጠሯቸው ቁጥራቸው 80 የሚደርሱ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ውስጥ ሃምሳ ያህሉን የዩክሬን አየር መከላከያ መትቶ መጣሉን የሃገሪቱ ጦር ሠራዊት አስታውቋል። ሰው አልባ አውሮፕላኖቹ ተመተው የወደቁት በቼርካሲ፣ ቼርኒሂቭ፣ ኬርሰን፣ ኪሮቮራድ፣ ኪቭ፣ ሚኮላይቭ፣ ኦዴሳ፣ ሱሚ እና ዚሂቶሚር መሆኑንም የዩክሬን አየር ኃይል አክሎ አመልክቷል። የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ በዛሬው ዕለት ‘ከሩስያ ድንበር አቅራቢያ ከሚገኘው የቤልጎሮድ ግዛት አቅራቢያ አንድ የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላን መትቼ’ ጥያለሁ ብሏል።
What's Your Reaction?