“ኢቲቱ” የተሰኘው አዲሱ የወተት ማርጊያ እርሾ ይፋ ሆነ
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በባዮቴክኖሎጂ ምርምር ያገኘውንና ወተትን ለማርጋት የሚያስችለውን “ኢቲቱ” የተሰኘ አዲስ የፕሮባዮቲክ እርሾ (Probiotic starter culture) ይፋ አደረገ
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በባዮቴክኖሎጂ ምርምር ያገኘውንና ወተትን ለማርጋት የሚያስችለውን “ኢቲቱ” የተሰኘ አዲስ የፕሮባዮቲክ እርሾ (Probiotic starter culture) ይፋ አደረገ።
ኢንስቲትዩቱ ይህንን አዲስ የምርምር ውጤት ይፋ ያደረገው፣ የዓለም የወተት ቀንን አስመልክቶ ዛሬ በተዘጋጀ የጋራ የውይይት መድረክ እና ዓውደ ርዕይ ላይ ነው።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ እንደገለጹት፤ “ኢቲቱ” የተሰኘው አዲሱ የፕሮባዮቲክ እርሾ በሀገሪቱ ያሉ የወተት ማቀነባበሪያ ድርጅቶች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማውጣት ከውጭ አገር አስገብተው የሚጠቀሙበትን እርሾ ሙሉ በሙሉ የሚተካ ነው።
ይህ የምርምር ውጤት የወተት ማቀነባበሪያዎችን የውጭ ምንዛሬ ወጪ ከመታደጉ ባሻገር፣ ፓስቸራይዝድ የተደረገ (የተቀቀለ) ወተትን በአራት ሰዓታት ውስጥ ብቻ ማርጋት እንደሚያስችል ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
ኢንስቲትዩቱ ምርምር ከሚያደርግባቸው የግብርና ምርቶች መካከል ወተትና የወተት ተዋጽኦዎች ዋነኞቹ መሆናቸውን የገለጹት ፕሮፌሰር ንጉሴ፤ አዲሱ ምርት ለምግብ ዋስትና እና ለጤና ተስማሚ የሆኑ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን አሟልቶ የያዘ መሆኑንም አብራርተዋል።
ኢንስቲትዩቱ የተሻሻሉ የሰብልና የእንስሳት ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት ለዘርፉ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ የጠቀሰው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘገባ፤ በአሁኑ ወቅትም በወተት ምርታማነት ላይ ትኩረት ያደረጉና በባዮቴክኖሎጂ የታገዙ ልዩ ልዩ ምርምሮች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አመልክቷል።
What's Your Reaction?