ኢንቨስትመንት ከቀረጥ ነፃ መብት መቅረት እና በኢኮኖሚው ላይ ያለው ተፅዕኖ
ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ለባለሀብቶች በጅምላ ስታበረክት የቆየችውንና ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ በ0% የግብር ነፃ መብት የሚሰጠውን አሠራር በይፋ ማክተሟን አስታውቃለች።
ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ለባለሀብቶች በጅምላ ስታበረክት የቆየችውንና ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ በ0% የግብር ነፃ መብት የሚሰጠውን አሠራር በይፋ ማክተሟን አስታውቃለች። መንግሥት ባወጣው አዲስ መመሪያ መሠረት፣ የሀገሪቱ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ በአፈፃፀም ላይ ወደተመሠረተ ጥብቅ የቁጥጥር ሞዴል የተቀየረ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ መስፈርቱን የሚያሟሉ ኩባንያዎች ሙሉ በሙሉ ነፃ ከመሆን ይልቅ እንደየዘርፋቸው ከ5% እስከ 15% የሚደርስ የተቀነሰ የድርጅት ግብር እስከ 10 ዓመታት ድረስ ብቻ እንዲከፍሉ ይደረጋል።
ይህ አዲስ ጥብቅ አሠራር መንግሥት ከኢንቨስትመንት ዘርፉ የሚያገኘውን ገቢ ለማሳደግና የባለሀብቶችን እውነተኛ አፈፃፀም ለመቆጣጠር ያለመ ቢሆንም፣ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ግን ጉዳዩ በደንብ ጥናት ሊደረግበትና ጊዜ ተወስዶ ሊታሰብበት እንደሚገባ ይጠቁማሉ።
ባለሙያዎቹ እንደሚያስረዱት ግብሩ ለመንግሥት የሚጨምረው ገቢ እንደ መንገድ፣ መብራት፣ መናፈሻ፣ ትምህርት ቤት እና ውሃ ያሉ መሠረታዊ ልማቶችን ለሕብረተሰቡ ለማቅረብ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ቢሆንም፣ በአንፃሩ ግን ባለሀብቶች የተጨመረውን አዲስ ግብር በምርትና አገልግሎት መሸጫ ዋጋ ላይ አክለው ስለሚያቀርቡ የሕብረተሰቡን የመግዛት አቅም በእጅጉ ሊፈታተነውና ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል የአገልግሎቶቹ ተጠቃሚ እንዳይሆን ሊያግደው ይችላል።
ከዚህም በላይ ፋብሪካዎችና ድርጅቶች የሚያመርቱት ምርት ተሸጦ የሚፈለገውን ያህል ግብ ካልመታ፣ ኢንቨስተሮቹ በቀጥታ ለኪሳራ ተጋልጠው ከገበያው እንዲወጡና አዳዲስ ባለሀብቶችም ወደ ዘርፉ እንዳይገቡ ትልቅ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎቹ ያሰምሩበታል።
What's Your Reaction?