የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ያላቸው የላቀ ሚና
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከአርባ በላይ ከሚሆኑ የማህበረሰብና የክልል መገናኛ ብዙሃን መሪዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ጋር እስካሁን ባከናወናቸው ተግባራትና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ የውይይት መድረክ እያካሄደ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከአርባ በላይ ከሚሆኑ የማህበረሰብና የክልል መገናኛ ብዙሃን መሪዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ጋር እስካሁን ባከናወናቸው ተግባራትና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ የውይይት መድረክ እያካሄደ ይገኛል። ኮሚሽኑ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አጀንዳ የማሰባሰብ ስራን በስፋት ሲሰራ መቆየቱን በዚሁ መድረክ ላይ ያመላከተ ሲሆን፣ በተለይም የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የጎላ ሚና እያበረከቱ መሆናቸውን አስታውቋል።
የኮሚሽኑ ክቡር ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በጉባዔው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኮሚሽኑ ስራውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለመሀበረሰቡ መረጃን በማጋራትና የኮሚሽኑን ተግባራት በማስረጽ ረገድ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን የነበራቸው አስተዋጽኦ የላቀ እንደነበር ገልጸዋል። አክለውም እነዚህ የሚዲያ ተቋማት ወደ ህዝቡ የቀረቡና በተለያዩ አገር በቀል ቋንቋዎች መረጃዎችን የሚያጋሩ በመሆናቸው፣ ምክክሩ አካታችና አሳታፊ እንዲሆን ከሃያ አምስት በላይ በሆኑ ቋንቋዎች መረጃዎችን ተደራሽ ሲያደርጉ መቆየታቸውንና ይህም መሰረት ላለው ሀገራዊ እድገት ቁልፍ አጋዥ መሆኑን ጠቁመዋል። ኮሚሽነሩ በቀጣይ ለሚደረገው ትልቁ ሀገራዊ ጉባዔም እነዚህ ተቋማት የተለመደ ግንባር ቀደም ሚናቸውን እንደሚወጡ ያላቸውን ሙሉ እምነት ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ በተለያዩ ሀገራት በተደረጉ ሀገራዊ ምክክሮች ወቅት የሚዲያ ሚና ምን ይመስል እንደነበርና በኢትዮጵያ ሂደት ውስጥስ ምን መሆን እንዳለበት የሚያስገነዝብ ጥናታዊ ጽሁፍ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪዎች ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። በዚህ በዓይነቱ ትልቅ በሆነው ጉባዔ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢን ጨምሮ የ32 የማህበረሰብ ሬድዮ ጣቢያዎች፣ የ7 ማህበረሰብ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች እና የ5 የክልል መገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
What's Your Reaction?