"ሞሰብ" ተንቀሳቃሽ አውቶቡስ የመንግሥት አገልግሎት ሥራ ጀመረ።

ከእንግዲህ የመንግሥት አገልግሎቶችን ለማግኘት በየቢሮው መንከራተትና በረጅም ወረፋ መንገላታት ታሪክ ሊሆን ነው።

Jun 29, 2026 - 16:54
 0  1
"ሞሰብ" ተንቀሳቃሽ አውቶቡስ የመንግሥት አገልግሎት ሥራ ጀመረ።



ከእንግዲህ የመንግሥት አገልግሎቶችን ለማግኘት በየቢሮው መንከራተትና በረጅም ወረፋ መንገላታት ታሪክ ሊሆን ነው። በአገር በቀል ባለሙያዎች የበለጸገውና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ያካተተው አዲሱ "ሞሰብ" ተንቀሳቃሽ አውቶቡስ፣ በርካታ የመንግሥት ተቋማትን አገልግሎቶች በአንድ ላይ አጠቃሎ ወደ ማኅበረሰቡ ብቅ ብሏል።

ይህ ዘመናዊ አውቶቡስ የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ፣ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር (TIN)፣ የንግድ ፈቃድ፣ የመንጃ ፈቃድ፣ የተሽከርካሪ ካርታ፣ የነዋሪነት መታወቂያ ዕድሳት እና የልደት ምዝገባን ጨምሮ በርካታ ወሳኝ ጉዳዮችን በአንድ ቦታ ላይ በፍጥነት ለማጠናቀቅ ያስችላል።

አውቶቡሱ ከፌደራል ተቋማት የመረጃ ማዕከላት ጋር በቀጥታ የተገናኘ ከመሆኑም በላይ የዲጂታል ወረፋ ማስተናገጃና የተለያዩ የዲጂታል ክፍያ አማራጮችን የያዘ በመሆኑ አስተማማኝና ቀልጣፋ አገልግሎት ይሰጣል።

በአሁኑ ወቅት በተጀመረው የሙከራ መርሃ-ግብር መሠረት አውቶቡሱን ሰኞና ማክሰኞ በመስቀል አደባባይ፣ እንዲሁም ረቡዕና ሐሙስ በቤተልና በዓለም ባንክ ማግኘት ይቻላል።

የቀጣይ ቀናትን መርሃ-ግብር ለመከታተል የሞሰብ ድረ-ገጽን መጎብኘት የሚቻል ሲሆን፣ ይህ አዲስ አሠራር ያረጀውን ቢሮክራሲ በመስበር የኅብረተሰቡን ጊዜና ገንዘብ በከፍተኛ ደረጃ ይቆጥባል ተብሎ ይጠበቃል።

የማዕከሉ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዮናስ አለማየሁ እንደተናገሩት "መሶብ በእኛ ሀገር ኢንጅነሮች የተሰራ የቴክኖሎጂ ፕላት ፎርም ሲሆን ባሶቹን ኮንበርት ስናደርግ  የተሳተፉት እነዚሁ ኢንጅነሮችና መካኒኮች ናቸው።
አገልግሎት ማሻሻልና ማሻገር ብቻ ሳይሆን የሀገር ውስጥ አቅም መጠቀም ላይ ትኩረት ያደረገ ማዕከል ሆኖ ተገኝቷል።  መሶብ በቀጣይ እየፈጠነ የሚሰፋ የቀጣይ አምስት አመቱ ትልቁ የመንግስት ስትራቴጂክ ፒላር ሲሆን በመንግሥት ላይ ሲነሳ የነበረውን የቅልጥፍና ቅሬታ ብቻ ሳይሆን ከሌብነት ጋር የሚያያዙ ጉዳዮችን የሚያስቀር ትልቅ ስራ ነው።" ብለዋል።

What's Your Reaction?

like

dislike

love

funny

angry

sad

wow