ኢትዮጵያ በቴምር ምርት ካላት እምቅ አቅም የለማው 1.2 በመቶ ያህሉ ብቻ ነው
ኢትዮጵያ ለቴምር ምርት ምቹ የሆነ ከ500 ሺህ እስከ 700 ሺህ ሄክታር የሚደርስ መሬት እንዳላት የግብርና ሚኒስቴር ገልጿል።
ኢትዮጵያ ለቴምር ምርት ምቹ የሆነ ከ500 ሺህ እስከ 700 ሺህ ሄክታር የሚደርስ መሬት እንዳላት የግብርና ሚኒስቴር ገልጿል።
ሆኖም ከዚህ ትሌቅ አቅም ውስጥ ግን የለማው 1.2 በመቶ ያህሉ ብቻ ነው።
የግብርና ሚኒስቴር አማካሪ ፕሮፌሰር ዓሊ መሐመድ እንዳሉት ሀገሪቱ ያላትን የቴምር ልማት አቅም በመጠቀም የውጭ ቴምር ጥገኝነትን በመቀነስ ወደ ወጪ ንግድ መሸጋገር ታስባለች።
የቴምር ልማትን ከተበታተነ ምርት ወደ ዘመናዊ የንግድ ሥርዓት ለማሸጋገር ያተኮረ የ10 ዓመት የምርምር እና ልማት እቅድ ቢኖርም እስካሁን ግን አመርቂ ውጤት አልተመዘገበም።
እቅዱ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ማስፋፋት፣ የተክል ቁሳቁስ ማባዛት፣ የመስኖ ሥርዓትን ማሻሻል፣ የማቀነባበሪያ ማዕከላትን መገንባት እና የወጪ ንግድ ጥራት ማረጋገጫን ያካተተ ነው።
በአፋር በተደረገ የምርምር ሥራ ከውጭ የመጡ እንደ ባርሂ እና ሜድጆል ያሉ ዝርያዎች የተሻለ ምርት ሊሰጡ እንደቻሉ አሳይቷል።
በጥናቱ ባርሂ በአንድ ዛፍ በዓመት 158.79 ኪሎ ግራም ምርት ሲሰጥ ሜድጆል 72.16 ኪሎ ግራም ሰጥቷል።
ይህ ግን የአንድ የምርምር ሙከራ ውጤት እንጂ የሁሉም የኢትዮጵያ እርሻዎች አማካይ ምርታማነት አይደለም።
የቴምር ምርት መስፋፋት ከምርት መጠን በተጨማሪ የሥራ ዕድልን ሊያሳድግ ይችላል።
የቴምር ምርት ከዛፍ ማልማት እስከ ማሰባሰብ፣ መለየት፣ ማሸግ እና ማቀነባበር ድረስ በርካታ የእሴት ሰንሰለት ሥራዎችን ይፈጥራል።
በተለይም ወጣቶችና ሴቶች በእነዚህ የምርትና የማቀነባበሪያ ሥራዎች ሊሳተፉ እንደሚችሉ የዘርፉ እቅድ ያመለክታል።
ይሁን እንጂ የቴምር ምርትን ወደ ወጪ ንግድ ለማሸጋገር የመሬት አቅም ብቻ በቂ አይሆንም።
የተሻሻሉ ዝርያዎች፣ የመስኖ ውሃ፣ የጥራት መለኪያ፣ የማከማቻና የማቀነባበሪያ አቅም እንዲሁም ከአምራች እስከ ገበያ ያለው ትስስር አስፈላጊ ይሆናል።
በአፋር ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከቴምር ምርታማነት ጋር በተያያዘ የተሻሻለ የምርት ቴክኖሎጂ፣ የተክል ቁሳቁስ እና የድህረ-ምርት አያያዝ እንደ ዋና ጉዳዮች ይነሳሉ።
ከመስከረም 10 እስከ 12 ቀን 2019 ዓ.ም በሰመራ እየተካሄደ ያለው ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የቴምር ፌስቲቫል አምራቾችን፣ ባለሀብቶችን፣ ተመራማሪዎችን እና የዘርፉን ተዋናዮች እንደሚያገኝ ይጠበቃል።
ይሁን እንጂ ፌስቲቫሉ ከተጠናቀቀ በኋላ የሚገኘው ውይይት ወደ ተጨባጭ ኢንቨስትመንት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የአምራቾች ድጋፍ እና የገበያ ትስስር መቀየር ይኖርበታል።
What's Your Reaction?