በሴትነታቸው የተገደሉ
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማት የወጡ ይፋዊ ሪፖርቶችና በቅርቡ የተካሄዱ ጥናቶች በኢትዮጵያና በሰሃራ በታች አፍሪካ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችና ግድያዎች ስር የሰደደ አሳሳቢ ቀውስ መሆናቸውን ያመለክታሉ።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማት የወጡ ይፋዊ ሪፖርቶችና በቅርቡ የተካሄዱ ጥናቶች በኢትዮጵያና በሰሃራ በታች አፍሪካ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችና ግድያዎች ስር የሰደደ አሳሳቢ ቀውስ መሆናቸውን ያመለክታሉ።
ዩኤን ዉሜን (UN Women) ከአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች የተገኙ መረጃዎችን መሠረት አድርጎ ባወጣው ጥናታዊ ሪፖርት መሠረት ከ2020/21 እስከ 2023/24 ባሉት ዓመታት ውስጥ ብቻ 139 ሴቶችና ህፃናት የታሰበበት ግድያ ተፈጽሞባቸዋል።
ከእነዚህ ሰለባዎች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት (83ቱ) በቀጥታ በሴትነታቸው ምክንያት የተገደሉ (Femicide) ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ግማሽ ያህሉ ህይወታቸውን ያጡት በፍቅር አጋሮቻቸው እጅ ነው።
ይሁን እንጂ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚያስጠነቅቁት በየቀኑ በይፋዊ ሪፖርት የማይመዘገቡ በግጭትና በፀጥታ ችግር ምክንያት ተደራሽ ባልሆኑ አካባቢዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ በመሆናቸው ይህ አሃዝ የወደፊቱን ትልቅ ቀውስ ከፊል እውነታ ብቻ የሚያሳይ ነው።
ይህ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ቀውስ በአህጉር ደረጃም በስፋት የሚስተዋል ሲሆን ከተጎጂዎች ቁጥር መብዛት አንጻር የሚቀርበው ተቋማዊና ማህበራዊ ድጋፍ እጅግ አናሳ መሆን ችግሩን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል።
የዩኒሴፍ (UNICEF) መረጃ እንደሚያሳየው በሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት 79 ሚሊዮን (22 በመቶ) የሚሆኑ ሴቶችና ልጃገረዶች ዕድሜያቸው 18 ዓመት ሳይሞላ አስገዳጅ ፆታዊ ጥቃት ወይም መድፈር ይፈጸምባቸዋል።
የችግሩ ስፋት ከፍተኛ ከመሆኑ ባሻገር በ2022 በኢትዮጵያ የተካሄደ ጥናት እንዳመለከተው ጥቃት ከደረሰባቸው ልጃገረዶችና ወጣት ሴቶች መካከል ከድርጊቱ በኋላ ተገቢውን እርዳታ፣ ህክምና ወይም ማህበራዊ አገልግሎት ማግኘት የሚችሉት ከአምስቱ አንዷ (20 በመቶ) ብቻ ናቸው።
የእነዚህን የጥናት ውጤቶች ተከትሎ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና የህግ ባለሙያዎች በፀጥታና በፍትህ ስርዓቱ ላይ አስቸኳይ የአሰራር ለውጥ እንዲደረግ እየጠየቁ ይገኛሉ።
ዋና ዋናዎቹ ጥያቄዎች ወንጀል ፈጻሚዎች በፍጥነት ተመርምረው ለፍርድ እንዲቀርቡና ለተጎጂ ቤተሰቦች የዘገየው ፍትህ በአስቸኳይ እንዲፋጠን እንዲሁም ለሴቶችና ህፃናት ደህንነት ፈጣን ምላሽ የሚሰጡ ጠንካራ የህግ ጥበቃ ስርዓቶች እንዲዘረጉ የሚያሳስቡ ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪም በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ከባድ ወንጀሎችን ማቃለል፣ ድርጊቱን በባህላዊ ሽምግልና ወይም በጊዜያዊ ስምምነት በማለፍ መደበኛውን የህግ አግባብ ማለፍ ሙሉ በሙሉ እንዲቆም እና ወንጀለኞች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ሙሉ የህግ ተጠያቂነት እንዲገጥማቸው ተሟጋቾቹ አጥብቀው እየጠየቁ ነው።
What's Your Reaction?