የአፍሪካ በዓለም አቀፍ የዕፅ ዝውውር ውስጥ እያደገ የመጣው ሚና ለአውሮፓ እና ለአሜሪካ ደህንነት ስጋት ጣለ

Nov 4, 2026 - 15:40
 0  3

አፍሪካ ከዚህ ቀደም የላቲን አሜሪካ ኮኬይን ወደ ተለያዩ አገራት የሚተላለፍበት መስመር ብቻ የነበረች ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ዋና የሎጂስቲክስ፣ የማከፋፈያ እና የሜታምፌታሚን (methamphetamine) ማምረቻ ማዕከልነት እየተቀየረች ይገኛል። 

የላቲን አሜሪካ የዕፅ ካርቴሎች ከአፍሪካ የወንጀል ድርጅቶች ጋር ያላቸውን አጋርነት እያሰፉ ሲሆን የአውሮፓ የወንጀል መረቦችም ከፍተኛ ትርፍ የሚያስገኙ የሸማች ገበያዎችን ለማግኘት የአፍሪካን መስመሮች በስፋት እየተጠቀሙበት ነው። 

በተለይም የሊቢያ እንደ ዕፅ ማስተላለፊያ ኮሪደርነት ሚና ማደግ እና በቱኒዚያ እየታየ ያለው የኮኬይን በቁጥጥር ስር መዋል፣ የዕፅ ዝውውሩ ከተለመደው የምዕራብ አፍሪካ መስመሮች አልፎ ወደ ሰሜን አፍሪካ እና ሜዲትራኒያን አካባቢ እየተስፋፋ መሆኑን ያሳያል። 

ዋናው ስጋት ደግሞ የተቀናጀ ወንጀል በአፍሪካ የፖለቲካ ተቋማት፣ የደህንነት መዋቅሮች እና በትጥቅ ቡድኖች የፋይናንስ ምንጭ ውስጥ እየሰረገ መግባቱ ሲሆን ይህም አህጉራዊ መረጋጋትን ከማናጋቱ ባሻገር ለአውሮፓ እና ለአሜሪካ አዲስ የደህንነት ስጋት ደቅኗል።

የዓለም አቀፍ የኮኬይን ምርት ካለፈው አስርት አመታት በአራት እጥፍ በመጨመር በአሁኑ ወቅት 4,100 ሜትሪክ ቶን የደረሰ ሲሆን አጠቃላይ የኢኮኖሚ እሴቱም ከ218 እስከ 374 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል።

በምዕራብ አፍሪካ በየዓመቱ በቁጥጥር ስር የሚውለው የኮኬይን መጠን በ2018 ከነበረበት 1 ሜትሪክ ቶን በቅርብ ዓመታት ወደ 30 ሜትሪክ ቶን አድጓል። 

ለአፍሪካ ሚና ማደግ ምክንያቶቹ የአውሮፓ ፍላጎት መጨመር፣ በተለመዱት የአትላንቲክ መስመሮች ላይ የተደረገው ጥብቅ ቁጥጥር እና በአንዳንድ የአፍሪካ አካባቢዎች ያለው ደካማ አስተዳደር ናቸው።

የብራዚሉ 'Primeiro Comando da Capital (PCC)' ከናይጄሪያ የወንጀል መረቦች ጋር ግንኙነት የፈጠረ ሲሆን፣ የሜክሲኮው 'Sinaloa' እና 'Jalisco New Generation (CJNG) ካርቴሎች ደግሞ በደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያ እና ሞዛምቢክ ውስጥ ከተገኙት የሜታምፌታሚን ማምረቻ ላቦራቶሪዎች ጀርባ እጃቸው እንዳለበት ይነገራል።

በተጨማሪም የጣሊያን 'Ndrangheta እና የባልካን ቡድኖች በኮኬይን ስርጭቱ ላይ በስፋት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ይህ የዕፅ ዝውውር መስፋፋት በሳህል እና በሰሜን አፍሪካ የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ቡድኖችን ይበልጥ ሊያጠናክር ይችላል ተብሎ ይፈራል። 

እንደ ጊኒ-ቢሳው እና ሴራሊዮን ያሉ ሀገራት የዕፅ ዝውውር፣  የፖለቲካ ሙስና እና የተቋማት መዳከም ግንኙነት ማሳያ ሲሆኑ፣ በደቡብ አፍሪካም ከተቀናጀ ወንጀል ጋር የተያያዙ ግድያዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። 

ትልቁ ስጋት ወንጀለኞቹ በሕግ አስከባሪዎች እና በፖለቲካ ውሳኔ ሰጪዎች ላይ ተፅዕኖ በማሳደር መንግስታዊ መዋቅሮችን መቆጣጠራቸው ነው። 

በመሆኑም ዋሽንግተን እና ብራሰልስ በሊቢያ፣ ቱኒዚያ፣ ናይጄሪያ፣ ሴራሊዮን እና ጊኒ-ቢሳው ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ በፋይናንስ ምርመራ፣ መረጃ መለዋወጥ እና የፀረ-ሙስና እርምጃዎች ላይ ከአፍሪካ ህግ አስከባሪዎች ጋር በትብብር መስራት እንዳለባቸው ተመልክቷል። 

ከ2027 እስከ 2030 ባሉት ዓመታት የሰሜን አፍሪካ መስመሮች ይበልጥ አስፈላጊ እንደሚሆኑና በአህጉሪቱ የወንጀል አጋርነቶች ይበልጥ እየጠነከሩ እንደሚሄዱ ይገመታል።

What's Your Reaction?

like

dislike

love

funny

angry

sad

wow