የጋሞ ዱቡሻ ዎጋን በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መደረሱ ተነገረ
አርባ ምንጭ — የጋሞ ብሔረሰብ የባህል፣ የሕግ እና የማኅበራዊ መስተጋብር መገለጫ የሆነውን "የጋሞ ዱቡሻ ዎጋ" በዓለም አቀፍ የላቀ ቅርስነት በዩኔስኮ (UNESCO) ለማስመዝገብ የተጀመረው ጥረት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱ ተገለጸ።
አርባ ምንጭ — የጋሞ ብሔረሰብ የባህል፣ የሕግ እና የማኅበራዊ መስተጋብር መገለጫ የሆነውን "የጋሞ ዱቡሻ ዎጋ" በዓለም አቀፍ የላቀ ቅርስነት በዩኔስኮ (UNESCO) ለማስመዝገብ የተጀመረው ጥረት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱ ተገለጸ።
የጋሞ ዞን ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ሞናዬ ሞሶሌ ከብስራት ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳስታወቁት፣ ቅርሱ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲመዘገብ የዞኑ ምክር ቤትና የአካባቢው ማኅበረሰብ ላነሱት ተከታታይ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ሰፊ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።
በዚህም መሠረት የዕጩነት ጥያቄው ለኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ቀርቦ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ፣ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ከዞኑ አስተዳደር፣ ከዞኑ ቱሪዝም መምሪያ፣ ከክልሉ ቱሪዝም ቢሮ እና ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር የተቀናጀ ጥናትና ምርምር ሲካሄድ መቆየቱን አስረድተዋል።
ባለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት በተዋቀሩ የባለሙያዎች ኮሚቴ አማካኝነት በዩኔስኮ ለመመዝገብ መሟላት ያለባቸውን መረጃዎች የመሰብሰብ ሥራ ሲከናወን የቆየ ሲሆን፣ የዚህ ጥናትና ምርምር ውጤት የመጨረሻው የትክክለኛነት ማረጋገጫ (Validation) መርሃ-ግብር ግንቦት 12 ቀን 2018 ዓ.ም መካሄዱን ኃላፊው አረጋግጠዋል። ይህም ለአጠቃላይ የምዝገባ ሂደቱ ስኬት ትልቅ ማሳያ መሆኑ ተገልጿል።
የጋሞ ዱቡሻ ማኅበረሰቡ በእኩልነት የሚዳኝበት፣ የኢኮኖሚ፣ የአንድነት እና የሰላም መገለጫ የሆነ ታላቅ ባህላዊ ተቋም ነው። በአካባቢው የሚነሱ ማናቸውም ግጭቶች አቅም ያለውም የሌለውም ሳይለይ ፍጹም ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የሚፈቱበትና እርቅ የሚወርድበት መድረክ መሆኑን የገለጹት አቶ ሞናዬ፣ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚስተዋሉ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ግጭቶችን ለመፍታት እንደ ዱቡሻ ያሉ የሀገር በቀል የውይይትና የእርቅ ሥርዓቶችን እንደ አርአያ መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል።
ይህ የምዝገባ ሂደት በተሳካ ሁኔታ ሲጠናቀቅ የጋሞ ዱቡሻ ዎጋ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም የሰው ልጅ የጋራ ቅርስ ሆኖ የሚመዘገብበት ዕድል ሰፊ መሆኑ ተመላክቷል።
What's Your Reaction?