18ኛው ዓመታዊ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጻሕፍት ዓውደ ርእይ ሊከፈት ነው

ባለፉት ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋና ግቢ ሲካሄዱ የነበሩት የመጻሕፍት ዓውደ ርእዮች ልክ እንደዚህ በደመቀ ሁኔታ፣ በታዋቂ ደራሲያን ወግና በአንባቢያን ተሞልተው ይታወቁ ነበር።

May 14, 2026 - 15:04
 0  1
18ኛው ዓመታዊ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጻሕፍት ዓውደ ርእይ ሊከፈት ነው

ባለፉት ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋና ግቢ ሲካሄዱ የነበሩት የመጻሕፍት ዓውደ ርእዮች ልክ እንደዚህ በደመቀ ሁኔታ፣ በታዋቂ ደራሲያን ወግና በአንባቢያን ተሞልተው ይታወቁ ነበር። ይህ የዕውቀት አውደ ርእይ ዘንድሮም ለ18ኛ ጊዜ ሲመለስ፣ ያንኑ የቀደመ ድምቀትና ለአንባቢ የሚመጥኑ መፅሐፍትን ይዞ ለመምጣት ተዘጋጅቷል።

በአገራችን የከፍተኛ ትምህርት ታሪክ ቀዳሚ የሆነው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ይህን  ታላቅ የመጻሕፍት ዓውደ ርእይ ከሰኔ 1 ቀን እስከ ሰኔ 7 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በዋናው ግቢ (ስድስት ኪሎ) እንደሚያካሂድ አስታውቋል።

​ይህ በጉጉት የሚጠበቀው ሳምንታዊ መርሃ ግብር፣ በሁሉም የዕውቀት ዘርፎች ላይ የሚያተኩሩ በርካታ ነባርና አዳዲስ መጻሕፍትን ለአንባቢያን የሚያቀርብ ሲሆን፣ የንባብ ባህልን ለማዳበርና በጸሐፍትና በአንባቢያን መካከል የሃሳብ ድልድይ ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

ለአሳታሚዎች የቀረበ ጥሪ

​ዩኒቨርሲቲው በዓውደ ርእዩ ላይ መሳተፍ ለሚፈልጉ የመጻሕፍት አሳታሚዎች እና አከፋፋዮች የቅድመ ምዝገባ ጥሪ አቅርቧል። በዝግጅቱ ላይ መሳተፍ የሚፈልጉ አካላት የሚከተሉትን መረጃዎች ልብ እንዲሉ ተብሏል፡-

​የመመዝገቢያ ቦታ፦ ስድስት ኪሎ በሚገኘው ዋናው ግቢ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ሕንጻ 1ኛ ፎቅ።

የመመዝገቢያ ጊዜ፦ ከግንቦት 10 እስከ ግንቦት 14 ቀን 2018 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ቀናት ዘወትር በሥራ ሰዓት።

የዓውደ ርእዩ ፋይዳ

​ይህ ዓመታዊ መድረክ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ከመላው አዲስ አበባና አካባቢዋ የሚመጡ የጥበብ ወዳጆች የፈለጓቸውን መጻሕፍት በአንድ ማዕከል እንዲያገኙ ዕድል ይፈጥራል።

በተለይም በዘንድሮው ዓመት በርካታ አዳዲስ የጥናትና ምርምር ሥራዎች እንዲሁም የሥነ-ጽሑፍ ውጤቶች ለዕይታና ለሽያጭ እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።

​መጻሕፍት የዕውቀት መቅጃ ቋቶች ናቸው፤ ይህ ዓውደ ርእይ ደግሞ ያንን ቋት ለሁሉም ተደራሽ የሚያደርግ ትልቅ የዕውቀት ድግስ ነው።

​አሳታሚዎች የተሰጣቸውን አጭር የምዝገባ ጊዜ ተጠቅመው ቦታቸውን እንዲይዙና ለዚህ ታላቅ ሀገራዊ የንባብ መድረክ ዝግጅት እንዲያደርጉ ተጋብዘዋል።

What's Your Reaction?

like

dislike

love

funny

angry

sad

wow