በአማራ ክልል ባለፉት 10 ወራት ከ200 በላይ እናቶች በወሊድ ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉ ተገለፀ

በአማራ ክልል ባለፉት አሥር ወራት ውስጥ ከ200 በላይ እናቶች በወሊድና ከወሊድ ጋር በተያያዙ የጤና ችግሮች ሕይወታቸው ማለፉን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

Jun 10, 2026 - 10:26
 0  8
በአማራ ክልል ባለፉት 10 ወራት ከ200 በላይ እናቶች በወሊድ ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉ ተገለፀ



የቢሮው የእናቶች ጤና ባለሙያ ዶክተር ኤርሚያስ አዱኛ እንደገለጹት፣ በወሊድ ምክንያት የሚከሰት የእናቶች ሞት በክልሉም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።

እ.ኤ.አ በ2010 ዓ.ም በክልሉ በዓመት 9 በመቶ የሚደርሱ እናቶች በወሊድና ከወሊድ ጋር በተያያዘ የጤና ችግር ሕይወታቸውን ያጡ እንደነበር ያስታወሱት ባለሙያው፣ በአሁኑ ወቅት የሞቱ እናቶች ቁጥር ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር እየቀነሰ ቢመጣም "አንዲትም እናት በወሊድ ምክንያት መሞት ስለሌለባት" ሕይወታቸውን ለመታደግ የተጀመሩት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በክልሉ በጤና ተቋማትና በሠለጠኑ ባለሙያዎች የወሊድ አገልግሎት የሚያገኙ እናቶች ቁጥር መጨመሩ፣ ለእናቶች ሞት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርገውን የደም መፍሰስ አደጋ አስቀድሞ ለመከላከልና ከተከሰተም እዚያው ሕክምና እንዲያገኙ ለማድረግ ከፍተኛ እገዛ አድርጓል።

በተጨማሪም ከዚህ ቀደም በሆስፒታሎች ብቻ የተለመደው የአልትራሳውንድ አገልግሎት በአሁኑ ወቅት በጤና ጣቢያዎችም ጭምር እየተሰጠ እንደሚገኝ ዶክተር ኤርሚያስ ገልጸዋል። በክልሉ ከሚገኙ 9 መቶ 40 ጤና ጣቢያዎች መካከል 4 መቶዎቹ በአሁኑ ወቅት የአልትራሳውንድ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

What's Your Reaction?

like

dislike

love

funny

angry

sad

wow