የዓለም ዘመናዊ ትምህርት ሥርዓት አመሠራረት እና ታሪካዊ ዕድገቱ
ዛሬ በዓለም ዙሪያ የምናየው የተደራጀ የትምህርት ሥርዓት ተማሪዎች በእድሜ ተከፋፍለው፣ በክፍል ደረጃ ተመድበው፣ በደወልና በሰዓት ተገዢ ሆነው ወጥ የሆነ ካሪኩለም የሚከታተሉበት አሠራር በድንገት የመጣ ሳይሆን በታሪክ ሂደት ውስጥ በተከሰቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጦች የተቃኘ ነው።
ዛሬ በዓለም ዙሪያ የምናየው የተደራጀ የትምህርት ሥርዓት ተማሪዎች በእድሜ ተከፋፍለው፣ በክፍል ደረጃ ተመድበው፣ በደወልና በሰዓት ተገዢ ሆነው ወጥ የሆነ ካሪኩለም የሚከታተሉበት አሠራር በድንገት የመጣ ሳይሆን በታሪክ ሂደት ውስጥ በተከሰቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጦች የተቃኘ ነው።
ከክርስቶስ ልደት በፊት በነበሩት የጥንታውያን ሥልጣኔዎች እንደ ግሪክ፣ ሮም፣ ቻይና፣ ሕንድ እንዲሁም በግብፅና በኢትዮጵያ በነበሩ የሃይማኖት ተቋማት ለትምህርት መሠረት ተጥሎ ነበር።
ሆኖም በዚህ ዘመን ትምህርት ለሁሉም ዜጋ ተዳራሽ ሳይሆን ለገዢው ፣ ለሃይማኖት አገልጋዮች ወይም ለፈላስፎች ብቻ የተወሰነ ነበር።
የመማር ማስተማር ሂደቱም በዋናነት ፍልስፍናን፣ ሃይማኖትንና ወታደራዊ ጥበብን ማእከል ያደረገ ነበር።
ለአሁኑ ዘመናዊ የትምህርት ሥርዓት ትልቁን መሠረት የጣለው በ18ኛው ክፍለ ዘመን በጀርመን በወቅቱ ፕሩሺያ የተዘረጋው የትምህርት ሞዴል ነው።
ፕሩሺያ በዓለም ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁሉንም ህጻናት የሚያሳትፍ የግዴታና ነፃ የመሠረታዊ ትምህርት ሥርዓት አስተዋወቀች።
ይህ ሞዴል የተዘጋጀው ወጥ ካሪኩለም፣ ብሔራዊ ፈተናዎች፣ የመምህራን ሥልጠናና ደረጃቸውን የጠበቁ ክፍሎችን በማካተት ነበር።
ዓላማውም መሠረታዊ ዕውቀትን ከመስጠት በተጨማሪ ሥርዓትንና ታዛዥነትን በዜጎች ዘንድ ማስረፅ ነበር።
በ19ኛው ክፍለ ዘመን የኢንዱስትሪ አብዮት በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ መስፋፋቱን ተከተሎ የፋብሪካዎች መብዛትና የቴክኖሎጂ ዕድገት ማንበብና መጻፍ የሚችሉ፣ ሰዓት የሚያከብሩና መመሪያ የሚከተሉ የሰው ኃይሎችን ፈለገ።
በዚህም ምክንያት የአሜሪካና የአውሮፓ አገራት የፕሩሺያን ሞዴል በሰፊው ተቀበሉት።
ትምህርት ቤቶችም ልክ እንደ ፋብሪካዎች ምርታማነትን ለማሳደግ በሰዓት ደወል፣ በደረጃ በደረጃ ትምህርትና በስታንዳርዳይዝድ ፈተናዎች እንዲመሩ ተደረገ።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የትምህርት አመለካከት ሙሉ በሙሉ ተቀየረ።
በ1948 እ.ኤ.አ በወጣው የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ዲክላሬሽን አንቀጽ 26 መሠረት ትምህርት የመሠረታዊ ሰብአዊ መብት አካል እንደሆነ ተደነገገ።
የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት UNESCO እና ሌሎች የዓለም አቀፍ አካላት ጥረት በመጨመር ትምህርት በአውሮፓና አሜሪካ ብቻ ሳይሆን በታዳጊ አገራትም ነፃና ተዳራሽ እንዲሆን ከፍተኛ እንቅስቃሴ ተደረገ።
በአሁኑ ዘመን የትምህርት አሠራር ከፍተኛ የለውጥ ሂደት ላይ ይገኛል።
የኢንተርኔት፣ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና የርቀት ትምህርት መስፋፋት ተማሪዎች ከክፍል ውጭ በራሳቸው ፍጥነትና ፍላጎት እንዲማሩ መንገድ ከፍቷል።
የዘመኑ ትምህርት ከሽመደዳ ይልቅ አመክንዮዊ አስተሳሰብ ፣ ችግር የመፍታት ብቃት እና የዲጂታል ክህሎቶችን ማሳደግ ላይ ያተኩራል።
What's Your Reaction?