የፈረንሳዩ ፍራንስ 24 ዘገባ እና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጠንካራ የተቃውሞ ምላሽ
ዓለም አቀፉ የዜና ማዕከል ፍራንስ 24 በኢትዮጵያ በተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እና በአዲስ አበባ የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ ያቀረበው ዘገባ “ከእውነት የራቀና ሚዛኑን ያልጠበቀ” ነው ሲል በፈረንሳይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በጽኑ ተቃወመ። ኤምባሲው ያወጣውን ይፋዊ መግለጫ ዋቢ በማድረግ አዲስ ማለዳ እንደዘገበው ፣ የፈረንሳዩ የዜና ማቅረቢያ ጣቢያ የቀረቡትን ሃሳቦች “አሳሳችና ወገንተኝነት የተሞላባቸው” ሲል ፈርጇቸዋል። በተለይም ዘገባው የሀገሪቱን ነባራዊ እውነታ እና የመንግስትን ሰፊ ጥረቶች ያላገናዘበ መሆኑን ኤምባሲው በምሬት ገልጿል።
ኤምባሲው በተለይ ፍራንስ 24 “በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ግማሽ ያህሉ የምርጫ ክልሎች አልመረጡም” በማለት ያሰራጨውን መረጃ ሙሉ በሙሉ ሐሰት ነው ሲል በአሃዛዊ መረጃዎች አስደግፎ አጣጥሎታል። ለአብነትም በአማራ ክልል ካሉ 138 የምርጫ ክልሎች ውስጥ ምርጫ ያልተካሄደው በ8ቱ (6 በመቶ) ብቻ መሆኑን በመጥቀስ የጣቢያውን ዘገባ ስህተትነት አጋልጧል። በተጨማሪም ምርጫው “የይስሙላ” ነበር መባሉንና የአፍሪካ ሕብረት እና የኢጋድ (IGAD) ታዛቢዎችን ሚና ለማሳነስ የተሄደበትን መንገድ የያዘው ዘገባ ፣ አንጋፋ ተቋማትንና መሪዎችን ለማጣጣል የተደረገ “የአስተሳሰብ አድሏዊነት” ማሳያ ነው ሲል ኮንኖታል።
በሌላ በኩል የፈረንሳዩ የዜና አውታር በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ያለውን የውበትና የመሠረተ ልማት ማዘመን ሥራዎችን “አስከፊ” ሲል መግለጹን ኤምባሲው ውድቅ አድርጎታል። ይህ የልማት ፕሮጀክት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት እየቀየረ ያለና በከፍተኛ ደረጃ አድናቆት የተቸረው ስኬት መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፣ ሚዲያው የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ስኬቶች ወደ ጎን በመተው አስተዳደሩን በ“እርስ በርስ ጦርነት” ብቻ ከፋፍሎ ለመግለጽ መሞከሩን ነቅፏል። በመጨረሻም የዚህ ምርጫ ውጤትና የሀገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው ከውጭ በሚሰጡ መግለጫዎች ሳይሆን በራሱ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መሆኑን ኤምባሲው አስታውቋል።
What's Your Reaction?