ሩሲያ አፍሪካውያንን በዩክሬን ግንባር ላይ እያሰለፈች ነው
የሩሲያ የደህንነት ተቋማት የውሸት የሥራ እና የትምህርት ዕድሎችን በመጠቀም በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያንን ወደ ዩክሬን ጦርነት ግንባር እየማገዱ መሆኑን አዳዲስ ሪፖርቶች አጋለጡ።
በሎሚ ኒውስ ዓለም አቀፍ ዜና ዴስክ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20/2018 ዓ.ም
ሩሲያ በዩክሬን እያካሄደች ባለው ጦርነት የደረሰባትን ከፍተኛ የወታደር እጥረት ለመሙላት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት አፍሪካውያንን በተደራጀ የማጭበርበር መረብ ወደ ግንባር እየማገደች መሆኑን አዳዲስ ዓለም አቀፍ የምርመራ ሪፖርቶች አያጋለጡ ።
እንደ INPACT እና የአፍሪካ ስትራቴጂካዊ ጥናት ማዕከል (Africa Center for Strategic Studies) የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ከ35 በላይ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ከ1,400 በላይ ዜጎች በሩሲያ የደህንነት ተቋማት (FSB) በተዘረጉ የውሸት መረቦች ተጠልፈው ጦርነቱ ውስጥ ገብተዋል።
የቀድሞ ተጎጂዎች እና የተፈቱ የጦር እስረኞች ምስክርነት እንደሚያሳየው፣ ወጣቶቹ ከሀገራቸው የሚወጡት በኢንተርኔት (በተለይም በቴሌግራም እና ዋትስአፕ) በሚለቀቁ ማስታወቂያዎች ተታልለው ነው። ማስታወቂያዎቹ ከፍተኛ ደሞዝ የሚያስገኝ የደህንነት ጥበቃ ሥራ፣ የቴክኒክ ሙያ፣ የነፃ ትምህርት ዕድል ወይም የስፖርት ውድድር አማራጮችን ያቀርባሉ።
ነገር ግን ተጎጂዎቹ ሞስኮ እንደደረሱ ፓስፖርታቸው እና ስልካቸው ይወሰድባቸዋል። በመቀጠልም ሙሉ በሙሉ በሩሲያኛ የተጻፈና የማይረዱትን ወታደራዊ ውል እንዲፈርሙ በዛቻና በኃይል ይገደዳሉ። ፈቃደኛ ያልሆኑት ደግሞ “የሞት ፍርድ ወይም እስራት” እንደሚጠብቃቸው ይነገራቸዋል። ከ3 ሳምንት ያነሰ አጭር ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ በቀጥታ ወደ ዩክሬን ግንባር ይላካሉ።
የምርመራ ሪፖርቶቹ እንደሚያሳዩት ሩሲያ እነዚህን አፍሪካውያን የምትጠቀመው “የሰው ሥጋ መፍጫ” (Meat-grinder) በተባሉ እጅግ አደገኛ የመጀመሪያ መስመር ጥቃቶች ላይ የዩክሬንን መከላከያ ሰብሮ ለመግባት ነው።
· ከተመለመሉት አፍሪካውያን መካከል ከ22% እስከ 42% የሚሆኑት በ4 ወራት ውስጥ ሕይወታቸው ያልፋል።
· በብዛት ከተጎዱት ሀገራት መካከል ግብፅ (361)፣ ካሜሩን (335)፣ ጋና (234) እንዲሁም ኬንያና ናይጄሪያ ይገኙበታል።
የአውሮፓ ፓርላማ በቅርቡ ባሳለፈው ውሳኔ ይህንን ድርጊት “ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና የሰዎች ዝውውር (Human Trafficking)” ሲል አውግዟል። በተመሳሳይ አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት (እንደ ደቡብ አፍሪካ) በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ዜጎቻቸውን ለማስመለስ እየሞከሩ ሲሆን፣ የካሜሩን መንግሥት ደግሞ ወታደሮቹ ወደ ሩሲያ እንዳይኮበልሉ የውጭ ጉዞ እገዳ ጥሏል።
የሎሚ ኒውስ ማስጠንቀቂያ፦ ወደ ሩሲያ የሚሄዱ ማናቸውንም መደበኛ ያልሆኑ የሥራ እና የቪዛ ማስታወቂያዎች ወጣቶች በጥንቃቄ ሊመረምሯቸው ይገባል!
What's Your Reaction?