ከእርዳታ ጠባቂነት ወደ ዓለም መሪነት፤ አፍሪካ የዓለምን የኢኮኖሚ ሚዛን የምትደፋበት አዲሱ የታሪክ ምዕራፍ
አፍሪካ በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ውስጥ የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ዋነኛ አንቀሳቃሽ ኃይል (Engine of Growth) ለመሆን የሚያስችላትን ዝግጅት እያጠናቀቀች መሆኑን የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ በይፋ አስታወቁ።
"ከእርዳታ ጠባቂነት ወደ ዓለም መሪነት፤ አፍሪካ የዓለምን የኢኮኖሚ ሚዛን የምትደፋበት አዲሱ የታሪክ ምዕራፍ"
ናይሮቢ — አፍሪካ በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ውስጥ የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ዋነኛ አንቀሳቃሽ ኃይል (Engine of Growth) ለመሆን የሚያስችላትን ዝግጅት እያጠናቀቀች መሆኑን የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ በይፋ አስታወቁ።
ሊቀመንበሩ ይህንን ያበሰሩት በኬንያ ናይሮቢ በተካሄደው ከፍተኛ የ"አፍሪካ ፎርዋርድ" (Africa Forward) ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ሲሆን፣ አህጉሪቱ ካላት እምቅ አቅም አንጻር ዓለም አቀፉን የኢኮኖሚ ሚዛን የመቀየር አቅም እንዳላት አፅንዖት ሰጥተዋል።
ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ከናይሮቢ ያበሰሩት የምስራች አህጉሪቱ የዓለምን ኢኮኖሚ ለመምራ ያላትን ሁለት ዋና ዋና ምሶሶዎች እንደሚከተለው አብራርተዋል፦
· ንቁ የወጣት ኃይል፦ አፍሪካ በዓለም ላይ በወጣት የሰው ኃይል ብዛት ቀዳሚ መሆኗን የገለጹት ሊቀመንበሩ፣ ይህ ምርታማ ኃይል በትክክል ከተመራ ለፈጠራና ለኢንዱስትሪ ዕድገት ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን ገልጸዋል።
· ያልተነካ የተፈጥሮ ሀብት፦ አህጉሪቱ ያላት ሰፊ የእርሻ መሬት፣ የማዕድን ሀብትና የታዳሽ ኃይል ምንጮች ለዓለም አቀፍ አቅርቦት ሰንሰለት ወሳኝ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ለኢኮኖሚ ሽግግር መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ማስፈልጋቸውን ጥቅሰው ለዘላቂ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን አህጉሪቱ የቤት ሥራዎቿን መሥራት እንዳለባት አሳስበዋል ለዚህም የሚከተሉትን ነጥቦች እንደ ዋና መፍትሔ አቅርበዋል፦
1. የካፒታል አጠቃቀም፦ የረጅም ጊዜ ካፒታልን ማሰባሰብና የውስጥ ሀብትን በአግባቡ ለልማት ማዋል ቀዳሚ ተግባር መሆን አለበት።
2. ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን መግታት፦ ከአህጉሪቱ የሚወጣውን ሕገ-ወጥ የገንዘብ ፍሰት በመከላከል፣ ያንን ሀብት ለመሠረተ ልማት ግንባታ ማዋል እንደሚገባ አሳስበዋል።
3. ቀጠናዊ ትስስር፦ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና (AfCFTA) ተግባራዊነትን በማፋጠን አገራት እርስ በርሳቸው ያላቸውን የንግድ ልውውጥ ማሳደግ አለባቸው ብለዋል
ማህሙድ አሊ ዩሱፍ በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይ "ሰላምና ደኅንነት ሳይረጋገጥ ስለ ልማት ማሰብ አይቻልም" በማለት፣ ፖለቲካዊ መረጋጋት ለኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት መሆኑን አስገንዝበዋል።
አፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት ለማረጋገጥና ድምጽዋ እንዲሰማ ካስፈለገ፣ አባል ሀገራት የፖሊሲ ቅንጅት ሊኖራቸውና ለአንድ ዓላማ በጋራ መቆም እንዳለባቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። ይህ ጉባኤ አፍሪካ ከመረዳት ወደ እራስን መቻል የምታደርገውን ሽግግር የሚያፋጥኑ አቅጣጫዎች የተቀመጡበት መሆኑም ተገልጿል።
What's Your Reaction?