የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያውያን ላይ ጥሎት የነበረውን የቪዛ ገደብ አነሳ
የአውሮፓ ኅብረት ከሁለት ዓመት በፊት በኢትዮጵያውያን ላይ ጥሎት የነበረውን ጥብቅ የቪዛ ገደብ ሙሉ በሙሉ ማንሳቱን አስታውቋል።
የአውሮፓ ኅብረት ከሁለት ዓመት በፊት በኢትዮጵያውያን ላይ ጥሎት የነበረውን ጥብቅ የቪዛ ገደብ ሙሉ በሙሉ ማንሳቱን አስታውቋል። ኅብረቱ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው፣ በሕገ-ወጥ መንገድ በአውሮፓ አገራት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ወደ አገራቸው ከመመለስ አንጻር የኢትዮጵያ መንግሥት ያሳየውን የተባባሪነት መሻሻል ተከትሎ መሆኑን የምክር ቤቱ መግለጫ ያመላክታል።
ከዚህ ቀደም ተጥሎ በነበረው እገዳ ምክንያት ኢትዮጵያውያን ለቪዛ የሚያስፈልጉ ቅድመ-ሁኔታዎችን በቀላሉ ማቃለል አይችሉም ነበር። በተጨማሪም ከሁለት ጊዜ በላይ የሚያገለግል የባለብዙ መግቢያ (Multiple-entry) ቪዛ እንዳይሰጥ ተከልክሎ የነበረ ሲሆን፣ የዲፕሎማቲክ ወይም የሰርቪስ ፓስፖርት ያላቸው ባለሥልጣናትም መደበኛ የቪዛ ክፍያ እንዲከፍሉ ይገደዱ ነበር።
የቪዛ ማመልከቻ ምላሽ የሚያገኝበት መደበኛ ጊዜም ከ15 ቀናት ወደ 45 ቀናት እንዲረዝም ተደርጎ ቆይቷል።
አሁን ላይ ግን ይህ የወጣው እገዳ በይፋ በመነሳቱ ለቪዛ አመልካቾች ትልቅ እፎይታን ይዞ መጥቷል።
ከዚህ በጎ የቪዛ ዜና ባሻገር፣ የአውሮፓ ኅብረት በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ምክንያት አቋርጦት የነበረውን የበጀት ድጋፍ ለኢትዮጵያ መንግሥት መልሶ ማነቃቃቱ የተገኘው ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ሌላው አካል መሆኑ ተገልጿል።
What's Your Reaction?