ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በባሌ ዞን የተከናወነውን የክረምት እርሻ አፈጻጸም ተመለከቱ

Nov 4, 2026 - 15:23
Nov 4, 2026 - 15:25
 0  3

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኦሮሚያ ክልል በባሌ ዞን የተከናወነውን የክረምት እርሻ አፈጻጸም በቦታው ተገኝተው መመልከታቸውን ገልጸዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት በዘንድሮው ክረምት ከፍተኛ የዝናብ እጥረት ሥጋት የነበረ ቢሆንም በመንግሥትና በሕዝብ የተቀናጀ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መልካም የሚባል አፈጻጸም መመዝገቡን ገልጸው ኢኮኖሚያችን አይበገሬ ሆኖ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ፈተናዎችን እንዲቋቋም ቀድሞ መዘጋጀትና አማራጮችን ማስፋት የግድ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ በቅርብ ዓመታት የጀመረችው የመስኖ ስንዴ ልማት ፕሮግራም በሀገር ውስጥ የምግብ ራስ-ምንጣትን ከማረጋገጥ ባለፈ በአህጉራዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ትኩረት ስቧል። 

ቀደም ሲል የሀገሪቱ የስንዴ ምርት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በዝናብ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ለድርቅና ለምርት መቀነስ ይጋለጥ የነበረ ቢሆንም በቆላማ እና ደጋማ አካባቢዎች የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በዓመት ሁለት እና ሦስት ጊዜ የማምረት አቅምን በመፍጠር አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍቷል።

በዚህም አሰራር ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት ከሚመረተው ጠቅላላ የስንዴ ምርት ከ60 በመቶ በላይ ድርሻ በመያዝ በመላው አፍሪካ አህጉር በግንባር ቀደምነት ከሚጠቀሱ አምራች ሀገራት ተሰልፋለች። 

ከዚህ ቀደም ለስንዴ ማስገቢያ በየዓመቱ ታወጣ የነበረውን በመቶ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ ሙሉ በሙሉ ማስቀረት የቻለችው ኢትዮጵያ እንደ FAO ባሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ዘንድም የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም እና ለቀጣናው የምግብ ዋስትና አስተዋጽኦ የሚያበረክት አርአያነት ያለው የግብርና ሞዴል እንደሆነች ይጠቀሳል።

What's Your Reaction?

like

dislike

love

funny

angry

sad

wow