አዲሱ የታክስ አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ምን ይዟል?
የገንዘብ ሚኒስቴር የነባሩን የታክስ አስተዳደር አዋጅ ክፍተቶች ለመሙላትና ሕጋዊ ተገዥነትን ለማስፈን ያዘጋጀውን አዲስ ረቂቅ አዋጅ ለባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ለውይይት አቅርቧል።
የገንዘብ ሚኒስቴር የነባሩን የታክስ አስተዳደር አዋጅ ክፍተቶች ለመሙላትና ሕጋዊ ተገዥነትን ለማስፈን ያዘጋጀውን አዲስ ረቂቅ አዋጅ ለባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ለውይይት አቅርቧል። ሚኒስቴሩ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በታክስና ጉምሩክ ሕጎች ላይ መሠረታዊ ለውጥ ለማድረግ ያቀደ ሲሆን፣ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ላይ የተካተቱት ዋና ዋና ማሻሻያዎች የሚከተሉት ናቸው፦
የታክስ ክሊራንስ እና ብድር፦ የፍርድ ቤት ክርክር ያለበት ግብር ከፋይ ያለበትን ዕዳ ለባንክ አሳውቆ ብድር ማግኘት የሚችልበት አሠራር ተዘርግቷል። እንዲሁም ባንኮችና የውጭ ባለሀብቶች ትርፍ ወደ ውጭ ከመላካቸው በፊት የታክስ ክሊራንስ ማቅረብ እንዳለባቸው የሚደነግገው መመሪያ ወደ አዋጅ ከፍ እንዲል ተደርጓል።
የቅሬታ አቀራረብና የስሌት ስህተት ማሻሻያ፦ ግብር ከፋዮች ከፍተኛ የይግባኝ ዋስትና (እስከ 75%) ሳይከፍሉ ጉዳያቸውን በገለልተኛ ተቋም በስምምነት የሚጨርሱበት አማራጭ ተፈጥሯል። በኦዲተሮች የሚፈጠሩ የስሌት ስህተቶች በግልጽ ታርመው አዲስ የውሳኔ ማስታወቂያ የሚሰጥበት ሥርዓት የተዘረጋ ሲሆን፣ የይግባኝ ጊዜውም ለተከታታይ 30 ቀናት ብቻ ሆኖ ተገድቧል።ወደኋላ ተመልሶ ግብር የመጠየቅ ገደብ፦ ቀደም ሲል የነበረው ገደብ የለሽ አሠራር ተቀይሮ፣ ያለማጭበርበር ለቀረ ታክስ እስከ 5 ዓመት፣ የማጭበርበር ድርጊት ከተገኘ ደግሞ እስከ 10 ዓመት ብቻ ወደኋላ ተሂዶ እንዲጠየቅ ሕጋዊ ገደብ ተጥሏል።
ጠንካራ የደረሰኝ ቅጣቶች፦ ደረሰኝ ባልተሰጠ ቁጥር በእያንዳንዱ ሰነድ 100,000 ብር አስተዳደራዊ ቅጣት ይጣላል። በአንድ የግብር ዘመን ውስጥ ጥፋቱ ለሦስተኛ ጊዜ ከተደገመ ደግሞ ከ5 እስከ 7 ዓመት ጽኑ እስራት ያስቀጣል። ሆኖም ሥራ አስኪያጆች አስተማማኝ የውስጥ ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋታቸውን ካረጋገጡ በሠራተኛ ጥፋት በጋራ ከመታሰር ነፃ ይሆናሉ።
What's Your Reaction?