የእየሩሳሌሙ የኤምባሲ እቅድ እና የሀርጌሳ-ሞቃዲሾ አዲስ የዲፕሎማሲ ፍጥጫ

የሶማሊላንድ መንግሥት በታሪኳ የመጀመሪያውን የውጭ ሀገር ኤምባሲ በእየሩሳሌም ልትከፍት መሆኑን ይፋ ማድረጓን ተከትሎ፣ በቀጠናው እና በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብና የፓለቲካ ትኩሳት ቀስቅሷል።

May 21, 2026 - 13:54
 0  2
የእየሩሳሌሙ የኤምባሲ እቅድ እና የሀርጌሳ-ሞቃዲሾ አዲስ የዲፕሎማሲ ፍጥጫ

የሶማሊላንድ መንግሥት በታሪኳ የመጀመሪያውን የውጭ ሀገር ኤምባሲ በእየሩሳሌም ልትከፍት መሆኑን ይፋ ማድረጓን ተከትሎ፣ በቀጠናው እና በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብና የፓለቲካ ትኩሳት ቀስቅሷል።

 እ.ኤ.አ. በ1991 ከሶማሊያ ተገንጥላ የራሷ መንግሥት፣ ገንዘብና የጸጥታ ኃይል ቢኖራትም እስካሁን በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ እውቅና ሳታገኝ የቆየችው ሶማሊላንድ፣ ባለፈው ታኅሣሥ ወር ነፃነቷን በይፋ በመቀበል የመጀመሪያዋ አገር በሆነችው እስራኤል ውስጥ ይህንን ውሳኔ ማሳለፏ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፋች ተደርጎ ተወስዷል። 

የሶማሊላንድ የመጀመሪያው ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ዶክተር መሐመድ ሐጂ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለእስራኤል ፕሬዚዳንት ይስሐቅ ሄርዞግ ያበረከቱ ሲሆን፣ በይፋዊ መልዕክታቸውም የሶማሊላንድ ኤምባሲ በእየሩሳሌም በቅርቡ እንደሚከፈትና በተመሳሳይ መልኩ እስራኤልም የራሷን ኤምባሲ በሀርጌሳ እንደምትከፍት በማረጋገጥ፣ ይህም በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን ስልታዊ ትብብር የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል። 

ይሁን እንጂ ይህ እርምጃ በሞቃዲሾው የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ዘንድ ከፍተኛ ቁጣንና የጠበቀ ውግዘትን ያስከተለ ሲሆን፣ የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ በሰጠው ይፋዊ መግለጫ “የሶማሊያ ሰሜን ምዕራብ ቀጠና” ሲል የጠራትን ሶማሊላንድ በእየሩሳሌም ኤምባሲ ለመክፈት ያደረገችው እንቅስቃሴ የሶማሊያን ሕጋዊ እና ፖለቲካዊ መዋቅር የሚጥስ፣ ከሕግ አንጻርም ሙሉ በሙሉ ዋጋ ቢስና ምንም ዓይነት ሕጋዊ ውጤት የሌለው ነው።" ሲል ውሳኔውን ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርጎታል። 

ይህ በሞቃዲሾና በሀርጌሳ መካከል የተፈጠረው የዲፕሎማሲ ፍጥጫ በሁለቱ ወገኖች ላይ ብቻ ሳይወሰን ወደ ዓለም አቀፍ ተቋማትም የተሻገረ ሲሆን፣ የእስልምና ትብብር ድርጅት (OIC) ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ የሶማሊላንድን ውሳኔ በጥብቅ በማውገዝ እርምጃው የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ፍላጎትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውሳኔዎችን የጣሰ ነው ማለቱ ተዘግቧል።

What's Your Reaction?

like

dislike

love

funny

angry

sad

wow