በኢትዮጵያ በየዓመቱ እስከ 8 ሺህ ሰዎች በኤችአይቪ እንደሚያዙ ተገለጸ። "ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል"
ህብረተሰቡ በተለይም ወጣቶች በሽታው አሁንም ከፍተኛ የመሰራጨት አቅም ላይ መሆኑን ተገንዝበው አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።
በኢትዮጵያ በየዓመቱ እስከ 8 ሺህ የሚደርሱ አዳዲስ ሰዎች በኤችአይቪ ቫይረስ እንደሚያዙ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። ህብረተሰቡ በተለይም ወጣቶች በሽታው አሁንም ከፍተኛ የመሰራጨት አቅም ላይ መሆኑን ተገንዝበው አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።
የኤችአይቪ/ኤድስ፣ የጉበት ቫይረስና የአባለዘር በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፈቃዱ ያደታ እንደገለጹት፤ ባለፉት አሥርት ዓመታት በተከናወኑ የመከላከል ሥራዎች የሞትና ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ ምጣኔ ቢቀንስም፣ በአሁኑ ወቅት ከ600 ሺህ በላይ ሰዎች ከቫይረሱ ጋር ይኖራሉ።
ከእነዚህ ውስጥ 550 ሺህ ያህሉ የፀረ-ኤችአይቪ መድኃኒት ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑት የቫይረሱን መጠን መቀነስ በመቻላቸው ጤናማ ሕይወት እየመሩ ይገኛሉ።
ሆኖም የሕክምናው ውጤታማ መሆን በማኅበረሰቡ ዘንድ "ኤችአይቪ አብቅቶለታል" የሚል አደገኛ መዘናጋት መፍጠሩን የጠቆሙት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ በተለይ በወጣቶች ዘንድ ያለው የግንዛቤ ክፍተት በሽታው አሁንም እንዲስፋፋ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ኮቪድ-19፣ ማርበርግና ኮሌራ ያሉ አጣዳፊ የጤና ስጋቶች መደጋገማቸውም ለኤችአይቪ የሚሰጠውን ትኩረት እንዲቀንስ እንዳደረገው አስታውሰው መጠንቀቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከዓለም አቀፍ ለጋሾች የሚገኘው የፋይናንስ ድጋፍ እየቀነሰ በመጣበት በዚህ ወቅት፣ ህብረተሰቡ ከራስ እስከ አገር ደረጃ የመከላከልና የጥንቃቄ ባህሉን በማጠናከር የበሽታውን ስርጭት ሊገታ እንደሚገባ ተመላክቷል።
What's Your Reaction?