በምስራቅ አፍሪካ የኢቦላ ወረርሽኝ ስጋት፡ ደቡብ ኮሪያ ጉዞዎች ላይ አስቸኳይ እገዳና ማስጠንቀቂያ ጣለች
በቀጣናው የኢቦላ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ፣ ደቡብ ኮሪያ ወደ ኡጋንዳ የሚደረግ ጉዞ ላይ ማስጠንቀቂያ መስጠቷን የዮንሃፕ የዜና አገልግሎት ዘገበ።
አዲስ አበባ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና አገር በሆነችው ኡጋንዳ እና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አዲስ የኢቦላ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከተሎ፣ የደቡብ ኮሪያ መንግስት ወደ ኡጋንዳ የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግና የጉዞ ደረጃውን ወደ “ልዩ የጉዞ ማሳሰቢያ” ከፍ ማድረጉን አስታወቀ። የደቡብ ኮሪያ ዜጎች ወደ ስፍራው የሚያደርጉትን ጉዞ በአስቸኳይ እንዲሰርዙም ጥሪ ቀርቧል።
የደቡብ ኮሪያው የዮንሃፕ የዜና አገልግሎት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ከዚህ ቀደም ለኡጋንዳ ተሰጥቶ የነበረው መደበኛ የደረጃ 2 የጉዞ ማስጠንቀቂያ ወረርሽኙን ተከትሎ ወደ “ልዩ የጉዞ ማሳሰቢያ” እንዲያድግ ተደርጓል። መንግስት የሀገሪቱ ዜጎች ወደ ኡጋንዳ ሊያደርጉት ያቀዱትን ማንኛውንም አይነት ጉዞ እንዲሰርዙ ወይም ለሌላ ጊዜ እንዲያስተላልፉ አጥብቆ አሳስቧል። በአሁኑ ወቅት በኡጋንዳ የሚገኙ የኮሪያ ዜጎችም ለደህንነታቸውና ለጤናቸው ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ መመሪያ ተላልፏል።
የሴኡል ጥብቅ እርምጃ በዚህ ብቻ አላበቃም፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኢቱሪ ግዛት ላይ እጅግ ከፍተኛ የሆነውን የደረጃ 4 የጉዞ እገዳ ለመጣል በሂደት ላይ መሆኑን ይፋ አድርጓል። በተመሳሳይ የደቡብ ኮሪያ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ኤጀንሲ (KDCA) ኮንጎን፣ ኡጋንዳን እና ጎረቤት ደቡብ ሱዳንን ለኢቦላ ቫይረስ በሽታ «ቅድሚያ የሚሰጣቸው የኳራንቲን አስተዳደር ሀገራት» አድርጎ በመሰየም በድንበር ኬላዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር መጀመሩን አስታውቋል።
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እና የወረርሽኙ ስርጭት ስፋት
የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) በቅርቡ ያወጣው ይፋዊ መረጃ እንደሚያሳየው፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተለይም በኢቱሪ እና በሰሜን ኪቩ ግዛቶች (በቡኒያ እና በጎማ ከተሞች) እስካሁን 51 የኢቦላ ተጠቂዎች በምርመራ ተረጋግጠዋል። ሁኔታውን ይበልጥ አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ ወረርሽኙ ድንበር ተሻግሮ ኡጋንዳ መግባቱ ነው። ኡጋንዳ በዋና ከተማዋ ካምፓላ ከኮንጎ የተጓዘ አንድ ሰው መሞቱን ጨምሮ ሁለት ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን በይፋ አረጋግጣለች።
What's Your Reaction?