"ወደ ካናዳ የሰራተኛ ስምሪት አልተጀመረም፤ የተጭበረበሩ ዜጎች አሉ" — ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን ወደ ካናዳ ለመላክ የተደረገውን ስምምነት ተገን በማድረግ፣ "ወደ ካናዳ እንልካችኋለን" በሚሉ ህገወጥ አካላት በርካታ ዜጎች የገንዘብ ማጭበርበር እየተፈጸመባቸው መሆኑን አስጠነቀቀ።

Jun 3, 2026 - 10:38
 0  7
"ወደ ካናዳ የሰራተኛ ስምሪት አልተጀመረም፤ የተጭበረበሩ ዜጎች አሉ" — ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን ወደ ካናዳ ለመላክ የተደረገውን ስምምነት ተገን በማድረግ፣ "ወደ ካናዳ እንልካችኋለን" በሚሉ ህገወጥ አካላት በርካታ ዜጎች የገንዘብ ማጭበርበር እየተፈጸመባቸው መሆኑን አስጠነቀቀ።

​ሚኒስቴሩ በቅርቡ ከካናዳው "ፊውቸር ፊት ኢንተርናሽናል" (Future Fit International) ከተሰኘ ድርጅት ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙን ተከትሎ፣ ሂደቱ የተጀመረ በማስመሰል ህገወጥ ማስታወቂያዎችን የሚያወጡና ገንዘብ የሚሰበስቡ አካላት መበራከታቸውን ገልጿል።
​በሚኒስቴሩ የውጪ ሀገር ሥራ ስምሪት የውል ምርመራ እና ማጽደቅ ዴስክ ኃላፊ አቶ በዛወርቅ ከተማ በሰጡት መግለጫ፣ "ወደ ካናዳ ሰራተኛ መላክ አልተጀመረም፤ ምንም ዓይነት ክፍያም የለም" ሲሉ ሂደቱ ገና በጥናት ላይ መሆኑን አረጋግጠዋል።

​ሂደቱ በጅማሮ ላይ ነው። መንግስት ከካናዳው ድርጅት ጋር የተፈራረመው "ባለሙያዎችን የመላክ ፍላጎት አለን" የሚል ስምምነት ላይ ብቻ ሲሆን ​እውቅና የተሰጠው ኤጀንሲ የሌለ መሆኑ ተነግሯል።  
​የቪዛ ጉዳይም ከራሱ ከካናዳ ኤምባሲ ውጭ ሌላ የቪዛ ወኪል አልተሰየመም።
​ክፍያን በተመለከተ ደግሞ ለዚህ ሂደት የሚጠየቅ ምንም ዓይነት ቅድመ ክፍያ የለም።

​ስምምነቱን ተገን በማድረግ በየማህበራዊ ሚዲያው በሚሰሩ ማስታወቂያዎች ተታልለው ገንዘባቸውን የተበሉ ዜጎች አቤቱታ ይዘው ወደ ሚኒስቴሩ እየመጡ መሆኑን አቶ በዛወርቅ አረጋግጠዋል። የተጭበረበሩ ሰዎችን ቁጥር በውል ባይገልጹም፣ ጉዳዩ ወደ ህግ መወሰዱን ግን ጠቁመዋል።

​"ገንዘብ አስከፍለዋቸው ተበልተው ወደ ሚኒስቴሩ የመጡ ዜጎች አሉ። በአሁኑ ወቅት ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመተባበር በእነዚህ ህገወጥ የገንዘብ ተቀባዮች ላይ ጥብቅ ክትትልና ምርመራ እየተደረገ ይገኛል" ያሉት አቶ በዛወርቅ ከተማ ​በመጨረሻም ሚኒስቴሩ፣ ወደፊት የመላክ ሥራው በይፋ ሲጀመር መንግስት እውቅና ያላቸውን ኤጀንሲዎች ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ገልጾ፤ ህብረተሰቡ አሁን ላይ ከሚደረጉ መሰል ህገወጥ የማጭበርበር ድርጊቶች ራሱን እንዲጠብቅ አሳስቧል።

What's Your Reaction?

like

dislike

love

funny

angry

sad

wow