በኢትዮጵያ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የስኳር በሽታ ምርመራ አሠራር ሊሻሻል እንደሚገባ ተጠቆመ

በኢትዮጵያ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የስኳር በሽታን (Gestational Diabetes) በጊዜ ለመለየትና ለማከም የሚያስችሉ የሕክምና አሠራሮችን በአስቸኳይ ማሻሻል እንደሚገባ ተጠቆመ።

Jun 3, 2026 - 11:43
 0  8
በኢትዮጵያ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የስኳር በሽታ ምርመራ አሠራር ሊሻሻል እንደሚገባ ተጠቆመ

በኢትዮጵያ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የስኳር በሽታን (Gestational Diabetes) በጊዜ ለመለየትና ለማከም የሚያስችሉ የሕክምና አሠራሮችን በአስቸኳይ ማሻሻል እንደሚገባ ተጠቆመ። ይህ የተጠቆመው በጥቁር አንበሳ፣ በጋንዲ መታሰቢያ እና በአበበች ጎበና ሆስፒታሎች ላይ የተደረገን ሰፊ ጥናት መነሻ በማድረግ ነው።

​በሕዝብ ጤና ትምህርት ቤት የስነ-ተዋልዶ፣ የቤተሰብ እና የሕዝብ ጤና ዲፓርትመንት ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር መሰለች አሰግድ ባደረጉት ጥናት ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) መመሪያዎች በሀገራችን በአግባቡ እየተተገበሩ አለመሆኑን አስታውቀዋል።

​የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው ዓለም አቀፍ ደረጃ መሠረት፦ ​ማንኛዋም ነፍሰ ጡር እናት ከ24ኛው እስከ 28ኛው ሳምንት ባለው የእርግዝና ጊዜ ውስጥ የስኳር በሽታ ምርመራ ማድረግ ይኖርባታል።
​ይህ ምርመራ የሕክምና ታሪክን ሳይለይ ለማንኛውም ነፍሰ ጡር እናት በደፈናው መደረግ እንዳለበት መመሪያው ይደነግጋል።
​ሆኖም በሀገራችን አሁንም ምርመራው የሚደረገው እናቶችን ለበሽታው ሊያጋልጡ የሚችሉ ግልጽ የጤና ችግሮች ወይም ምልክቶች ሲታዩ ብቻ እንደሆነ ዶ/ር መሰለች በጥናታቸው ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

 ከ28 ሳምንት በላይ በሆኑ ቁጥራቸው ከ1,050 የሚበልጡ እናቶች ላይ የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው፣ መመሪያው ቢኖርም በተግባር ላይ የዋለው ግን በጣም በጥቂት እናቶች ላይ ብቻ ነው።
​የችግሩ ስፋት እና የሚያስከትለው ጉዳት
​በጥናቱ መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ በእርግዝና ወቅት በስኳር በሽታ የሚጠቁ እናቶች ቁጥር 12 በመቶ ገደማ የሚጠጋ በመሆኑ፣ ምርመራው ለሁሉም እናቶች ያለ ልዩነት ተደራሽ መሆን አለበት ተብሏል። ህመሙ በጊዜ ካልተገኘ በአጭርና በረጅም ጊዜ በእናትና በሕፃኑ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል።

​በሕፃኑ ላይ የሚደርሱ አፋጣኝ ችግሮችን ስንመለከት ​ከወሊድ በኋላ የሕፃናት የመተንፈስ ችግር ማጋጠም
​የሰውነት ሙቀትን በራሳቸው መቆጣጠር አለመቻል ስሆን የተለያዩ ​የረጅም ጊዜ የጤና ስጋቶቹም ​ሕፃናቱ ሲያድጉ እንዲሁም እናቶች ከወሊድ በኋላ በቋሚነት በስኳር በሽታ (Type 2 Diabetes) የመያዝ ዕድላቸውን የሚያሰፋ ከመሆኑም በላይ፣ በልብ ጤና ላይ ከፍተኛ ችግር ያስከትላል።

​የእናቶችንና የሕፃናትን የረጅም ጊዜ ጤና ለመጠበቅ፣ የጤና ተቋማት ነፍሰ ጡር እናቶች ክትትል በሚጀምሩበት ወቅት የሳምንት እርግዝናቸውን እያዩ የቅድመ-ምርመራ አሠራሩን የግዴታ ሊያደርጉት እንደሚገባ በጥናቱ ማጠቃለያ ላይ ተመልክቷል።

What's Your Reaction?

like

dislike

love

funny

angry

sad

wow